ኢኒስቲትዩቱ በቆዳ ዘርፍ ያለበትን የባለሞያ እጥረት ለማቃለል ያበረከተው አስተዋጽኦ የሚበረታታ ነው-የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
አዲስ አበባ, መጋቢት 3 ቀን 2002 (አዲስ አበባ) - የኢትዮጵያ ቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢኒስቲትዩት ባለፉት ዓምስት ዓመታት በቆዳ ዘርፍ ያለበትን የባለሞያ እጥረት ለማቃለል ያበረከተው አስተዋጽኦ የሚበረታታ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

ኢኒስቲትዩቱ በቀጣይ አምስት ዓመትም ከቆዳው ዘርፍ ወጪ ንግድ በጥቅሎ 500 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት የሚያስችለውን ዕቅድ ነድፏል፡፡

የምክር ቤቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ቋሚ ኮሚቴ የኢኒስትዩቱን የአምስት ዓመታት የስራ አፈጻጸም ሪፖርትን ገምግሞ ባቀረበው የማጠቃለያ ሪፖርት እንደገለጸው በዘርፉ የሰለጠነ ባለሞያ ለማፍራት ከአጫጭር ስልጠናዎች ጀምሮ እስከ መጀመሪያ ዲግሪ ድረስ የትምህርት ስርዓት ዘርግቶ ባለሞያ እያፈራ ነው፡፡

ይህም በአጭር ጊዜ ውስጥ መንግስት ብሎም ኢኒስቲትዩቱ የያዘውን ተልዕኮ ለማሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የቋሚ ኮሚቴው አባላት በአስተያየታቸው ገልጸዋል፡፡

ኢኒስቲትዩቱ በቀጣይም በአሁኑ ጊዜ እጥረት የታየበትን የምርምርና ስርጸት ስራ በተጠናከረ መልኩ መስራት እንደሚኖረበትም ጠቁመዋል፡፡

የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሪክተር አቶ ወንዱ ለገሰ እንደገለጹት ባለፉት አምስት ዓመታት በቆዳ አመራረት፣ በጫማ፣ በቆዳ አልባሳትና ዕቃዎች ቴክኖሎጂ፣ 520 ተማሪዎች ከፍተኛ ሰርተፊኬት፣ 700 ተማሪዎች ደግሞ በ10 ሲደመር 3 መርሃ ግብር ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

እንዲሁም በቆዳ አመራረት ቴክኖሎጂ 30 ተማሪዎች የጀመጀመሪያ ዲግሪ 45 ተማሪዎች ደግሞ አጫጭር ስልጠና አግኝተዋል፡፡

በኢኒስቲትዩቱ ድጋፍ እየተደረገላቸው ወደ ውጭ ከሚልኩ ድርጅቶችም በአመት እስከ 100 ሚሊዮን ደላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ እየተገኛ መሆኑንና በቀጣይ አምስት ዓመትም በጥቅሎ 500 ሚሊዮን ዶላር ከቆዳው ዘርፍ ወጪ ንግድ ይገኛል ተብሎ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም አሁን የሚላከውን 16 ሚሊዮን የቆዳ ውጤቶች ወደ 39 ሚሊዮን ለማድረስ ታቅዷል፡፡

ስ.2.30 የ.5.55 ሪ.6.00 ያ.6.42 ኤ10፡29

---END---

Headlines
ፕሬዚዳንት ግርማ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የማላዊ አምባሳደርን አሰናበቱ
ፓርቲዎች ሦስተኛ ዙር የምርጫ ክርክራቸውን አካሄዱ
ሴቶችን በህገ መንግስታዊ መብቶቻቸው ተጠቃሚ ለማድረግ ሰፋ ያለ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው
ኢኒስቲትዩቱ በቆዳ ዘርፍ ያለበትን የባለሞያ እጥረት ለማቃለል ያበረከተው አስተዋጽኦ የሚበረታታ ነው-የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
ዓለም አቀፉ የግላኮማ ቀን ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ታስቦ ዋለ
(c) The Ethiopian News Agency