አስተዳደሩ የከተማዋን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሳደግ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ ይቀጥላል-ከንቲባው
አዲስ አበባ, መጋቢት 3 ቀን 2002 (አዲስ አበባ) - የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ወደ 80 በመቶ ለማሳደግ የሚያደርገው እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባው አስታወቁ።

ከንቲባው አቶ ኩማ ደመቅሳ ትናንት የከተማዋን የመጠጥ ውሃ ችግር ለማቃለል ከሚያስችሉት ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነውን የአቃቂ የጥልቅ ውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ ፕሮጀክት ከጎበኙ በኋላ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት አስተዳደሩ የከተማዋን የውሃ እጥረት ለማቃለል የሚያደርገውን ጥረት ይገፋበታል።

አስተዳደሩ የነዋሪዎችን የመጠጥ ውሃ ችግር ለማቃለል ካለፈው ዓመት ጀምሮ በአቃቂ ከርሰ ምድር 40 ጥልቅ ጉድጓዶችን ቁፋሮ እያከናወነ መሆኑን መሆኑንና እስካሁን የተገኘው ውጤት አበረታች ነው ብለዋል።

በአካባቢው በተደረገ የሙከራ ቁፋሮ በቂ ውሃ መኖሩን ተረጋግጧል ያሉት ከንቲባው፣እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ የውሃ አቅርቦቱን ሽፋን ከ52 በመቶ ወደ 73 ለማድረስ መቻሉን አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ተክሌ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በቀን 73ሺህ ሜትር ኩብ ውሃ ለማምረት የሚያስችል መሆኑን ገልጸው፣ቁፋሮአቸው ከተጀመሩት 15 የውሃ ጉድጓዶች መካከል የአሥሩ መጠናቀቁን አስረድተዋል።

ከጉድጓዶቹ የሚገኘውን ውሃ ወደ መሐል ከተማ ለማጓጓዝ የሚያስችል 18 ኪሎ ሜትር የመሥመር ዝርጋታና አምስት ሺህ ሜትር ኩብ ውሃ መያዝ የሚያስችል ማጠራቀሚያ ግንባታ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ መናገራቸውን የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።

---END---

Headlines
በጅማ ከተማ ምርጫ ክልል የሚወዳደሩ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መሰረቱ
በጅማ ዞን የመራጮችና እጩዎች ምዝገባ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ
አስተዳደሩ የከተማዋን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሳደግ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ ይቀጥላል-ከንቲባው
(c) The Ethiopian News Agency