የኢጋድ የፖርላማ ሕብረት ጽህፈት ቤትን ለማጠናከር የልማት አጋር ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠየቀ
አዲስ አበባ, የካቲት 1 ቀን 2002 (አዲስ አበባ) -

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት/ኢጋድ/ የፖርላማ ሕብረት ጽህፈት ቤትን ለማጠናከር የልማት አጋር ድርጅቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ የሕብረቱ ምክትል ፕሬዚዳንት አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ጠየቁ፡፡

በአዲስ አበባ አዲስ ስለተቋቋመው የሕብረቱ ጽህፈት ቤት አላማዎች የልማት አጋር ድርጅቶች በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው ጽፈት ቤቱን ለማጠናከር የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚረዳ የውይይት መድረክ ዛሬ ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ እና የኢጋድ ፓርላማ ህብረት ምክትል ፕሬዚዳንት አምባሳደር ተሾመ ቶጋ እንደገለጹት ምንም እንኳን የሕብረቱ ጽህፈት ቤት አዲስ አበባ ተቋቁሞ ሥራ ቢጀምርም ስለመቋቋሙም ሆነ ስለ አላማዎቹ እንዲሁም ምን አይነት ድጋፍ ማሰባሰብ እንደሚገባ በደንብ አይታወቅም ነበር፡፡

በመሆኑም አዲስ አበባ ተቀማጭ ለሆኑ የልማት አጋሮች የሕብረቱን አላማዎች፣ አደረጃጀት፣ አሰራርና ሕብረቱ በአሁኑ ወቅት ያሉበትን ችግሮች ለመግለጽና ከነሱ የሚጠበቀው ድጋፍ ምን እንደሆነ ለማስገንዘብ ውይይቱ መካሄዱን ገልጸዋል፡፡

የሕብረቱ ጽህፈት ቤት አዲስ አበባ መሆን ለሕብረቱ በርካታ ጥቅም እንደሚያስገኝ ጠቁመው የልማት አጋሮች፣ የዲፕሎማቶችና የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ በመሆኗ ከአጋሮች ጋር በሚሰሩት ስራዎች የሕብረቱን አላማ በማሳወቅ ረገድ ምቹ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሕብረቱ ዋና ጽህፈት ቤት አዲስ አበባ ውስጥ መቋቋሙ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሚና ላይና ኢትዮጵያ በአፍሪካ የምትጫወተውን ሚና ከግምት ያስገባ መሆኑን ጠቁመው ይህም አገሪቱ ተጨማሪ የቀጠና ጽህፈት ቤቶችንና አህጉራዊ ተቋትን ለማስተናገድ ያላትን ብቃት የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡

የሕብረቱ አላማዎችም በቀጠናዋ ያለውን የሰላም፣ የፀጥታና ያለመረጋጋት ችግር በመፍታትና በሕዝቦች መካከል ያሉትን ግጭቶች በመፍታት ረገድ ፓርላማው ሚና መጫወት አለበት፣ መንግስታት የሚሰሯቸውን የመሠረተ ልማት ሥራዎች ማገዝና ድጋፍ መስጠት እንዲሁም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር የሚሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የሕብረቱ ዋና ፀሃፊ ቦራን ዳውድ አህመድ እንደገለጹት ወደፊት ሕብረቱ ለክፍለ አህጉሩ የኢኮኖሚ ትስስር፣ የተፈጥሮ ሃብት መጋራት፣ የአባል አገራቱን ሕዝቦች ለማገናኘት የሚያስችል የመሠረተ ልማት ግንባታ እንዲሁም የገበያ እድሎችን በማስፋት ከፍተኛ እድገት ለማምጣት ይረዳል፡፡

አባል አገራቱ በጋራ በመስራት በክፍለ አህጉሩ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመከላከልና መፍትሄ ለመሻት ከቻልን የምጣኔ ሃብትና የማህበራዊ እድገት በማምጣት ድህነትን ሙሉ በሙሉ ለመቀነስ እንችላለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሕብረቱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠርም በ2010 ቅድሚያ ሰጥቶ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከልም የሕብረቱን መዋቅር ሂደት ማጠናቀቅ፣ ቋሚ የፓርላማ ኮሚቴዎችን ማቋቋም፣ በተለያዩ ዘርፎች ለሚከናወኑ ተግባራት ፕሮጀክቶችን መንደፍ የሚሉት እንደሚገኙበት ጠቁመዋል፡፡

ሕብረቱን ወደተሻለ ደረጃ በማድረስ በአፍሪካ ልማት ውስጥ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች የበኩሉን ሚና እንዲያበረክት የልማት አጋሮች የድርሻቸውን እንደሚወጡ ያላቸውን እምነትም ለተሰብሳቢዎቹ ገልጸውላቸዋል፡፡

አጋሮቹ በሰጡት አስተያየት ስለ ሕብረቱ በቂ እውቀት እንዳልነበራቸው ጠቁመው አሁን ግን አላማውን በደንብ መረዳታቸውን ጠቁመዋል፡፡

የሕብረቱ አላማም ትክክለኛ መሆኑን ገልጸው ለአላማው መሳካት ድጋፍ እንደሚሰጡም ተናግረዋል፡፡

ተሰብሳቢዎቹ የሕብረቱ አባል አገራት አምባሳደሮች፣ በገንዘብ ድጋፍ ሊያደርጉ የሚችሉ እንደ የአውሮፓ ሕብረት፣ የጃፓን፣ የቻይና፣ የመካከለኛው ምስራቅ የልማት አጋሮች፣ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን፣ ከጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝና ከሌሎች አገራት የተውጣጡ ተወካዮች ናቸው፡፡

---END---

Headlines
የኢጋድ የፖርላማ ሕብረት ጽህፈት ቤትን ለማጠናከር የልማት አጋር ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠየቀ
(c) The Ethiopian News Agency