አዲስ አበባ, ሰኔ 26 ቀን 2001 (አዲስ አበባ) - ላለፉት 46 ዓመታት እስልምና ኃይማኖት ትምህርት በማስተማርና በርካታ የመስጊድ ኢማሞችን በማፍራት የሚታወቁት ሺህ መሐመድ ራፊዕ ቡሴሪ ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ ። ሺህ መሐመድ ራፊዕ ቡሴሪ በቀድሞ ወሎ ክፍለ አገር ልዩ ስሙ ቀጠጣይ ደይሉ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ከእናታቸው ከወይዘሮ ማዲቱ አብደላ እና ከአባታቸው ከአቶ ራፊዕ ቡሴሪ በ1903 ዓ.ም ተወለዱ።
ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ከታዋቂ ሙፍቲዎች መሠረታዊ የኃይማኖት ትምህርት ተምረዋል።
በሳውዲ አረቢያና በሱዳን ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን ለ16 ዓመታት በሳውዲ አረቢያ ከተለያዩ የዓለም ክፍል የመጡ ተማሪዎችን አስተመረዋል።
ሺህ መሐመድ ራፊዕ ቡሴሪ በተለያዩ ሀገራት በመማር ማስተማር ያገኙትን ልምድ ወደ አገራቸው ተመልሰው ለ46 ዓመታት ለአገራቸውና ለኃይማኖታቸው መጎልበት አስተዋጽኦ አበርክተዋል ።
በተለይ በኃይማኖት መቻቻልና መከባበር ላይ ለኅብረተሰቡ አርዓያ ከመሆናቸው በተጨማሪ በኢትዮጵያ ውስጥ በማስተማር ላይ የሚገኙ የመስጊድ ኢማሞችን ያፈሩ የኃይማኖት አባት ናቸው ።
ሼህ መሐመድ ቡሴሪ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ዛሬ በሰኔ 26 ቀን 2001 ዓ.ም በተወለዱ በ98 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል ።
የሼህ መሐመድ ራፊዕ ቡሴሪ የቀብር ሥነሥርዓት ነገ በታላቁ አንዋር መስጊድ ጸሎት ከተካሄደ በኋላ ከቀኑ በሰባት ሰዓት በኮልፌ የሙስሊሞች መካነ መቃብር እንደሚፈጸም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ዛሬ ማምሻውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጿል
ሪ 1፡30 ኤ2 2፡00 ጥአ ጠሰድ 0፡30
---END---