አሜሪካ የአፍሪካን የምጣኔ ሃብት እድገት የማስፋፋት ፍላጐት አላት-የአሜሪካ ዋና የንግድ ባለሥልጣን
አዲስ አበባ, ሰኔ 26 ቀን 2001 (አዲስ አበባ) - አሜሪካ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት ዋነኛ አላማው የአፍሪካን የምጣኔ ሃብት እድገት ማስፋፋት መሆኑን የአሜሪካ ዋና የንግድ ባለሥልጣን አስታወቁ፡፡

የአሜሪካ ረዳት የንግድ ተወካይ ፍሎሪዚሊ ሊሰር እንደገለጹት ከዓለም አቀፍ የንግድ ድርሻ ውስጥ የሰብ ሰሃራ አፍሪካ ድርሻ ከሁለት በመቶ ያነሰ ነው፡፡

የሰብ ሰሃራ አፍሪካ አገራት የንግድ ድርሻቸውን ከአንድ እስከ ሦስት በመቶ ማሳደግ ቢችሉ በዓመት የ70 ቢሊዮን ዶላር የኤክስፖርት ገቢ ማግኘት እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

ይህም በአሁኑ ወቅት ለአገራቱ ከሁሉም ለጋሾች ከሚደረግላቸው ድጋፍ በሦስት እጥፍ ብልጫ ይኖረዋል ያሉት ፍሎሪዚሊ የአፍሪካን ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ለማፋጠን ንግድ ቁልፍ ሚና ያለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የንግድ ተወካይዋ እንዳሉት ከአህጉሪቱ በዋነኛነት ፔትሮሊየም፣ ማእድናት፣ ካካዎና ቡና ኤክፖርት የሚደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

እንዲሁም በሌሎች የአለም አገሮች ምጣኔ ሃብትን ለማሳደግና ድህነትን ለመቀነስ የሚያስችል ሆኔታ በአህጉሪቱ መኖሩን አመልክተዋል፡፡

ግብርና የአፍሪካ ጠንካራ መሠረት ቢሆንም ዘርፉ በኤክስፖርትና በንግድ ዘርፎች የሚፈለገውን ያህል አስተዋጽኦ አለማበርከቱንም አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም በተለይ የግብርና ምርቶችን በከፍተኛ ዋጋ ኤክስፖርት ማድረግ በአህጉሪቱ የምግብ ዋስትናን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

እንደ አውሮፖ አቆጣጠር በ2000 የአሜሪካ የንግድ ሕግ ውስጥ ለአፍሪካ አገራት ከቀረጥና ኮታ ነፃ የንግድ እድል/አጐዋ/ መመቻቸቱ አሜሪካ ከሰብ ሰሃራ አፍሪካ ጋር ያላትን የንግድ ልውውጥ በመጠንና በአይነት ለማሳደግ መሳሪያ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በኤክስፖርት ንግድ የመጠንና የዓይነት መጣጣም በአህጉሪቱ የረጅም ጊዜ የምጣኔ ሃብት ልማትና እድገት ለማምጣት እንደሚያስችል የሚያምኑ መሆናቸውን ባለሥልጣኗ ተናግረዋል፡፡

በአሜሪካና በሰብ ሰሃራ አፍሪካ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ እንደ አውሮፖ አቆጣጠር በ2008 ብቻ 104 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር አመልክተዋል፡፡

ይህም በ2001 አጐዋ ተግባራዊ መደረግ በጀመረበት የመጀመሪያ ዓመት ከነበረው ከሦስት እጥፍ በላይ መድረሱን ያመለክታል ብለዋል፡፡

በቀጣይም አሜሪካ የአጐዋ እድል ተጠቃሚ አገራትን ቁጥር አንዲሁም አገራቱ በአሜሪካ ገበያ የሚያቀርቡትን ምርት አይነትና ጥራት ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ለማሳደግና የአፍሪካን ተወዳዳሪነት ለማጠናከር በዘርፉ ብርቱ ጥረት እንደሚደረግ አመልክተዋል፡፡

ሪ፡3፡30፣ያ፡9፡58 ኤ10፡43 ጠሰድ7፡13 ተ10፡43

---END---

Headlines
ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ የሳዑዲ ዓረቢያ የሕክምና ቡድን አባላትን አነጋገሩ
አሜሪካ የአፍሪካን የምጣኔ ሃብት እድገት የማስፋፋት ፍላጐት አላት-የአሜሪካ ዋና የንግድ ባለሥልጣን
ውጤታማ የሕብረት ሥራ ማኅበራት፣ ዩኒየኖችና ባለሙያዎች ሊሸለሙ ነው
(c) The Ethiopian News Agency