አዲሰ አበባ, ሰኔ 26 ቀን 2001 (አዲስ አበባ) - ባለፉት አራት ዓመታት ከጠበቀ ወዳጅነት ወደ ጥልቅና ፍሬያማ የትብብር ጥምረት የተሸጋገረው የህንድና ኢትዮጵያ ግንኙነት በያዝነው ክፍለዘመን ውጤታማ ከሚባሉት የሃገራት ግንኙነቶች ተርታ ሊያሰልፈው እንደሚችል በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አስታወቁ፡፡በኢትዮጵያ ውስጥ እየተመዘገበ ያለው ለውጥ ሃገሪቱ የሚሊኒየም የልማት ግቦችን ለማሳካት በሚያስችላት ደረጃ ላይ አንደምትገኝ አመላካች ነው ብለዋል፡፡
አምባሳደር ጉርጂት ሲንግ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበራቸውን የአራት አመታት የስራ ጊዜ ማጠናቀቃቸውን አስመልክተው ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት ህንድና ኢትዮጵያ የደረሱበት የኢኮኖሚ ትብብርና የሁለትዮሽ ግንኙነት ዘረፍ ከፍተኛ ወደሚባል ደረጃ ተሸጋግሯል፡፡
ኢትዮጵያ ለህንድ በጣም አስፈላጊና ስትራተጂካዊ ጠቀሜታ ያላት ሃገር ናት ያሉት አምባሳደሩ ወደፊትም ይህንን ግንኙነት በአፍሪካ ውስጥ ትልቁን ሰፍራ የሚይዝ ለማድረግ የህንድ መንግስት እንደሚጥርም አስታውቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ ያለው የሀንድ ቀጥታ ኢንቨሰትመንት መጠንን አስመልክተው ሲናገሩም በኢትዮጵያ ያሉት 439 የህንድ ኩባንያዎች በ4ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል በተለያዩ የግል የኢንቨሰትመንት ተግባራት ላይ መሰማራታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ይህም ከሌሎች ሃገራት ጋር ሲነጻጸር ትልቁ የቀጥታ ኢንቨስትመንት አካል መሆን የቻለና መቶ በመቶ እድገት ያሳየ የሃገራቱ የተሳካ ግንኙነት መገለጫ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያና የህንድ የንግድ ሚዛን አሁንም ወደህንድ የሚያጋድል ቢሆንም ዋናው ጉዳይ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ግንኙነቱን ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር ነው ብለዋል፡፡የንግድ ሚዛን መዛባቱ የሀንድ ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ ሊያመርቱ ፍቃድ የወሰዱበት የፖታሽ ማዕድን ማውጣት ስራ ሲጠናቀቅ መቶ በመቶ ሊቀረፍ የሚችል ችግር ነው ብለዋል፡፡
''በኢትዮጵያ በቆየሁበት ጊዜ ለኔ ትልቁ አላማ የሃገራቱን የላቀ የወዳጅነት ጥምረት ወደጠንካራ የደቡብ ደቡብ የኢኮኖሚ ግንኙነት መለወጥ ነበር፡፡ይህም ተሳክቶልኛል'' ብለዋል አምባሳደሩ- በአሁኑ ወቅት ሃገራቱ የደረሱበት የሁለትዮሽ ግንኙነት ጠንካራ መሰረት የያዘ መሆኑን ሲናገሩ፡፡
ኢትዮጵያና ሀንድ በፖለቲካው መስክ ተመሳሳይ አቋም የሚያራምዱ ሃገራት እንደመሆናቸው በአሸባሪነት ላይ ያላቸው አቋም ግልጽና ቀጥተኛ ነው ያሉት አምባሳደሩ ይህም አሸባሪነትን ለመዋጋት በሚካሄደው አለም አቀፍ ትግል ላይ በጋራ እንዲሰሩ አስችሏቸዋል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ህንድ የኢትዮጵያን የተማረ የሰው ሃይል ለመገንባት ከምትሰጠው የነጻ ትምህርት እድልና በየጊዜው የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ከሚጓዙት ባለሙያዎች ባሻገር የህንድ ባለሙያዎችም ወደዚህ ሃገር እየመጡ በተለያዩ መስኮች ላይ ያላቸወን እውቀት እንዲያካፍሉ በመደረግ ላይ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በፖለቲካውና በኢኮኖሚው መስክ ውጤት ማምጣት የሚችል ብልህ አመራር ያላት ሃገር መሆኗን ገልጸው በቆይታቸው የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን ላደረጉላቸው ትብብርና የወዳጅነት አቀባበል የላቀ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
---END---